ForeverMissed
Large image
His Life
May 15, 2021
የኢንጂነር ተክለጻዲቅ አበራ አጭር የሕይወት ታሪክ

ኢንጂነር ተክለጻዲቅ አበራ ከአባታቸው ከአቶ አበራ ሳህሌ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ አልማዝ አሳመረ ጥቅምት 27 ቀን 1962 ዓ.ም በአዲስ አበባ ልዩ ስሙ አማኑኤል በሚባለው አካባቢ ተወለዱ፡፡ እድሜአቸው ለትምህርት ሲደርስ በቄስ ት/ቤት ገብተው ከፊደል አስከ ዳዊት ንባብ ድረስ ከዘለቁ በኋላ በየካቲት 23 1ኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ከ 1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኮልፌ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተምረው በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋኩሊቲ በመግባት በሲቪል ምህንድስና ተመርቀዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት ካጠናቀቅ በኋላ ወደ ሥራ ዓለም በመግባት በአድማስ ኮንስትራክሽንና በሳትኮን ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ከሳይት መሀንዲስነት እስከ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅነት አገልግለዋል፡፡ በተለይም በሳትኮን ኮንስትራክሽን ቆይታቸው

1ኛ. የሰቆጣ ሆሰፒታል ግንባታ በፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅነት

2ኛ. በጅጅጋ የመምህራን ማሰልጠኛ ግንባታ በፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅነት

3ኛ. በመቀሌ፤አድዋ፤ አክሱምና ሽሬ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ ጣቢያ // ሰብ ሰቴሽን/ ግንባታ የሁሉም ፕሮጀክቶች ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሰርተዋል፡፡

እነዚህን ፕሮጀክቶች ሲመሩ እድሜአቸው ከ 30 ዓመት በታች የነበረ ሲሆን ባላቸው የሥራ ቁርጠኝነት፤ አመራርና አፈጻጸም ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ከበላይ አለቆቻቸው ልዩ ክብርና አድናቆት ይሰጣቸው የነበሩ ትጉህ ሠራተኛ ነበሩ፡፡

1991 ዓ.ም ጀምሮ የግላቸውን ታብኮ ኮንስትራክሽን የተባለ ድርጅት በመክፈት ሥራ የጀመሩ ሲሆን በዚህም ቆይታቸው እስከ ሕይወት ህልፈት ድረስ በሚወዱት ሙያቸው ቤተሰቦቻቸውን፤ ወገኖቻቸውን፤ ህዝባቸውንና አገራአቸውን በቅንነት አገልግለዋል፡፡ በግል መስራት ከጀመሩ ወዲህ ከ300 በላይ የመኖሪያ ቤቶች፤ ከ20 በላይ የንግድ ህንጻዎች፤ በሚዛን ቴፒ እና ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቶች፤ በቤቶች ልማት የ20/80 እና 40/60 ፕሮጀክቶች፤ በህዝባዊና ልማት ድርጅት ፕሮጀክቶች ላይ በብዙ የተሳተፉ፤ ለብዙ ወገኖች የሥራ እድል የፈጠሩ፤ የሥራ ሥነ-ምግባርና መርሆዎችን አክብረው የሚሰሩ ታላቅ አገር ወዳድ ሰው ነበሩ፡፡

ኢንጂነር ተክልጻዲቅ አበራ በዚሁ ሁሉ የሥራ ኃላፊነት ውስጥ እያሉ እንኳን  ለመማር ካለቸው ጽኑ ፍላጎት ትምህርታቸውን በመቀጠል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሀይድሮሎጂ ኢንጂነሪንግ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ኢንጂነር ተክለጻዲቅ አበራ በማኅበራዊ ሕይወታቸውም እጅግ መልካም የነበሩ ሲሆን በአካባቢ ልማት፤ በወላጅ አልባ ህጻናትና አረጋውያን እንክብካቤ፤ በአብያተ ከልርስቲያናት ግንባታ እጅግ የላቀ ተሳትፎ ያደርጉ ነበር፡፡

ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ ለሰዎች መታየትን ካለመፈለጋቸው የተነሳ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ሁሉንም መግለጽ ባይቻልም በቁጥር በውል የማይታወቅ ወላጅ አልባ ልጆችና አራጋውያንን ይረዱ ነበር፡፡

ከአብያተ ክርስቲያናት ግንባታ ከብዙ በጥቂቱ

1ኛ. በሰሜን ሸዋ ዞን በእንሳሮ ወረዳ የምትገኘው የሐመረ ኖኅ ጠገራ ቅድስት ማርያም ቤ/ክ በእውቀታቸው፤ በሙያቸውና በገንዘባቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ የሰሩ ሲሆን አሁንም ከዚህ ቀደም ተሰርቶ የነበረው ቤ/ክ በመጥበቡና በማርጀቱ እንደገና በመሰራት ላይ ላለው ቤ/ክ ከዲዛይን ጀምሮ በሙያና በገንዘብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ እየሰሩ የነበሩ ሲሆን ለአገልጋዮችም በዘላቂነት ወርሃዊ ደሞዝ በመክፈል ያስገልግሉ ነበር፡፡

2ኛ. በሰሜን ሸዋ ዞን በመርሐቤቴ ወረዳ የመሳኖ አይኔ ሜዳ ቅዱስ ሚካኤል ቤ/ክ በሙያቸውና በገንዘባቸው ሰርተዋል በዘላቂነትም አገልጋዮች የሚያስፈልጋቸውን በማሟላት እንዲገለገል አድረገዋል፡፡   

3ኛ. በአዲስ አበባ አገረ ስብከት የቀበና መድሐኔዓለም ቤ/ክ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በዋና አማካሪነት አገልግለዋል በግንዘባቸውም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

4ኛ. በአዲስ አበባ አገረ ስብከት የአያት ጌቴ ሴማኒ ቅድስት ኪዳነ-ምህረትና ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ የቴክኒክ ኮሚቴ በመሆን ግንባታው አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ በገንዘባቸውም በሙያቸውም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ኢንጂነር ተክለጻዲቅ አበራ በዚህ ጽሁፍ ያልተካተቱ በርካታ ሥራዎችን የሰሩ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡

ኢንጂነር ተክለጻዲቅ አበራ በትዳር ሕይወታቸውም ከወ/ሮ አልማዝ እሸቱ ጋር ላለፉት 22 ዓመታት በፍቅርና በመከባበር ለሌሎች አርአያ የሚሆን የትዳር ዘመንን አሳልፈዋል፡፡ በዚህ ዘመናቸውም ከባለቤታቸው ጋር በመሆን ታናናሽ ወንድምና እህቶቻቸውን እንደ አባት አስተምረው እንደ ወንድም መክረው ከፍ ላለ ቁምነገርና ሕይወት አብቅተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አምስት ሴትና አንድ ወንድ ልጅ ኣሳድገው አስተምረው ለከፍተኛ ተምህርትም አብቅተዋል፡፡

ኢንጂነር ተክለጻዲቅ አበራ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፤ ሰውን የሚያከብሩ፤ መልካን የሚሰሩ፤ ብዙ ከመናገር ብዙ መስማትና መስራት የሚያዘወትሩ መልካም የእግዚአብሔር ልጅ ነበሩ፡፡

በዚህ ዓለምም ስትኖሩ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ ያለውን አምላካዊ ቃል ፈጽመው በሥጋውና ደሙ ታትመው የከበሩ በመሆናቸው እረፍት እንጂ ሞት የለባቸውምና ወደ ዘላለም ቤታቸው ወደ ቸሩ አባታቸው ወደ እግዚአብሔር ሄደዋል፡፡

ኢንጂነር ተክለጻዲቅ አበራ ምንም እንኳን ከዚህ በላይ ቢቆዩና ከዚህም በላይ ብዙ መልካም ሥራ እንዲሰሩ ብንመኝም አምላክ ፈቃዱ የሆነው የቆይታቸው ጊዜ ይህ ነውና ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ51 ዓመታቸው የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለመ-ድካም አርፈው የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም በደ/ም/ቅ/ሰአሊተ ምሕረትና ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ካቴድራል ቤተሰቦቻቸው፤ ያገለገሉባት ቤ/ክ አገልጋይ አባቶች ካህናትና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በታላቅ ክብር ሥርዐተ-ረፍታቸው ተፈጽሟል፡፡                            



ነፍሴ ሆይ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፤ እግዚአብሔር መልካም አድረጎልሻልና፤ ነፍሴን ከሞት ዓይኔንም ከእንባ እግሬንም ከመሰናክል አድኖአልና በሕያዋን አገር በእግዚአብሔር ፊት እሄዳለሁ መዝ. 115 ፡ 7-9