Text read at the ceremony by Mr.Yeraswork Admassie ( Amharic version )
March 3, 2021
by Emyu Gessese
የአቶ ታደሠ ገሠሠ ትውስታ
ወንድማችን ታደሠ ገሠሠ ሰኔ 14 ቀን 1933 ዓ/ም ከእናቱ ከወ/ሮ የሺሐረግ ይርዳውና ከአባቱ ከአቶ ገሠሠ
ተድላ በአዲስ አበባ ከተማ ጎላ ሰፈር ተወለደ፡፡ የተወለደው ሀገራችን ነፃነቷን መልስ በተቀዳጀት ማግሥት ከወር
ተኩል በኋላ ብቻ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም ወላጆቹ “ታደሠ” ብለው የሰየሙት።
ታደሠ፣ ሰባት ዓመት እስከሚሆነው ድረስ ሐረር ከተማ በአያቱ ሰፊ ቤት ከእህቱና ከአጎትና አክስት ልጆቹ ጋር
በደስታ አደገ።
ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርቱን በሊሴ ገብረማርያም ት/ቤት ተከታተለ፡፡
ወጣቱ ታደሠ በአገር ቤት ትምህርቱ መጨረሻ ላይ፣ በ1952 ዓ/ም በኮንጎ ነፃ መውጣት ሳቢያ የተፈጠረውን
ብጥብጥ ለማርገብ ወደዚያ የተላከውን የኢትዮጵያ ጦር በአስተርጓሚ ኦፊሴርነት ተቀላቅሎ በመዝመት፣
እስከ ሕይወቱ መጨረሻ የዘለቀውን አና መለያ ጠባዩ የሆነውን ማኅበረሰባዊ አክቲቪዝም “ሀ” ብሎ ጀመረ።
ከሊሴ ገብረማርያም ከተመረቀ በኋላ የነፃ ትምህርት እድል አግኝቶ በፓሪስ ከተማ በሚገኘው ዕውቁ
ዩኒቨርስቲ በመግባት የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ተከታትሎ የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀበለ። በመቀጠልም
በሌላው ዕውቅ ኤኮል ሱፔሪየር ጂ ኢኮኖሚ ሁለተኛ ዲግሪነውን በኢኮኖሚክስ ሰራ፡፡ በመቀጠልም ለሁለት
አመታት በዚያው በፖራል በማኔጅመንትና በኢንፎርሜሽን የሥራ ዘርፍ ተሰማርቶ ልምድ አካበተ።
በአውሮፓ/ ትምህርቱን በመከታተል ላይ በነበረበት ጊዜ ከትምህርቱ በተጓዳኝ፣ ሃገሩንና አህጉሩን በተመለከተ
በወቅቱ በነበሩ እንቅስቃሴመ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በተለይ፤
1ኛ/ በአውሮፓ የኢት ተማሪዎች ማኅበር የመፅሄት ቦርድ አባል
2ኛ/ በፈረንሳይ የኢት ተማሪዎች ማኅበር ሥራ አ/ኮሚቴ አባል
3ኛ/ በፖሪስ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር ሥ/አ/ኮማቴ አባል ሆኖ አገልግሏል፡፡
በተጨማሪ፡- በፈረንሳይ የአፍሪካ ተማሪዎች ማኅበር አመራር ውስጥ አባል ሆኖ ወደ ሁዋላ በየአገሮቻቸው
ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ካሳደሩ ወጣት አፍሪካውያን ጋር ጎን ለጎን ሆኖ ሠርቷል።
ታደሠ፣ ከአውሮፓ ቆይታው በጉዋላ ወደ ውድ ሃገሩ ተመልሶ በተለያዩ መንግሥታዊ፣ ዓለም አቀፋዊ እና
መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ መደበኛ ሠራተኛ በመሆን ለሁለት ዓሠርተ-ዓመታት አገልግሏል።
ከነዚህም መሥሪያ ቤቶች ዋናዎቹ፡-
- የየካቲት 66 የት/ቤት
- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
- በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የቴክስታይል ኮርፖሬሽን
- በአ/አ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኮሚሽን መሥሪያ ቤት ሲሆኑ በተጨማሪ በዝምባቡዌ
አህጉራዊ የሸማቾች መስሪያ ቤት አገልግሏል።
ከኢ-መደበኛ ሥራ ውጭም በትርፍ ጊዜው በበርካታ የማኅበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ አስተዋጽኦ አድርጉዋል።
ከነዚህም ዋና ተጠቃሾቹ የሚከተሉት ናቸው-።
- የኢትዮጵያ ቼስ ፎደሬሽን መስራች እና ለረዥም ጊዜ የአመራሩ አባል፤
- የቡል ጨዋታ በኢትዮጵያ እንዲለመድ ሲል የቡል ክለቦች መስራች እና አነቃቂ፤
- የኩላሊት ማጠቢያ መሳሪያ በብዛት ወደ ሃገር በማስገባት ረገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወተው የኩላሊት
ሕሙማን መርጃ ማህበር አመራር አባል፤
- የሮተሪ ክለብ ንቁ አባል፤ እና
- ከአዲስ አድማስ መስራቾች እና መሪዎች አንዱ ነበር።
በተጨማሪ፤ ታደሠ አራት መፃሕፍት እና በርካታ መጣጥፍ ደርሶ አሳትሟል። ከነዚህም ውስጥ ሁለቱ
በጤና እና በጤናማ አመጋገብ ላይ ያተኰሩ ጠቃሚ መፃሕፍት ናቸው።
ታደሰ የቤተሰብ ሰው፥ ቁምነገረኛ እና ለወዳጅ ዘመዱ ቀደሞ ደራሽ፥ የዕርዳታ ሥራ ቀስቃሽ እና አደራጅ
የነበረ ሲሆን፤ የዚያኑ ያህል ደግሞ የደስታ እና የጨዋታ ሰው በመሆን በራሱ ጭምር የመቀለድ ተሰጥዎ
ያለው ነበር።
ዛሬ ወንድማችን ታዴን የምንሰናበት ቀን ነው። ሆኖም በመለያዬታችን የምናዝንበት ብቻ ሳይሆን፥ ረዥም
ፍሬያማ ህይወቱን የምንዘክርበትና ለቤተሰቡ መፅናናትን እና መልካሙን የምንመኝበት አጋጣሚ ነው።
ስለሆነም፥ ለመላ ወዳጅ ዘመዱ፤ በተለይም ለባለቤቱ ወ/ሮ አማረች ክፍሌ፥ ለእህቱ ወ/ሮ ምንትዋብ፥
ለልጆቹ ሊድያ፣ መብአ፣ የሺሃረግ፣ ሕሩይ እና እሙዬ፤ እንዲሁም ለሦስቱ የልጅ ልጆቹ ፈጣሪ መፅናናትን
እንዲሰጣቸው እና እንዲጠብቃቸው እንመኛለን።
በመጨረሻ፤ ጊዜ የጣለብን ወረርሽኝ እስከሚወገድ ድረስ ቀናቶችን በጥንቃቄ ለማሳለፍ ስለምንገደድ፤
የስንብቱን ሥርዓቱን በዚሁ ቋጭተን መበተን የኖርብናል። ትናንትና ማታ ላይ ባለቃ ጊዜ ለዛሬ ተዘጋጅቶ
የነበረውን የጠበል ፀዲቅ ሥርዓት በዚህ ህሳቤ እንዲሰረዝ እንደተደረገው፤ ለሃዘነተኛው ቤተሰብ ደህንነት
በማሰብ ሃዘናችንን ለመግለፅም ሆነ ለማፅናናት ወደ ቤተሰቡ መኖሪያ በመሄድ ቆይታ ከማድረግ
እንድንቆጠብ አደራ እንላለን።
ቤተሰቡ፤ በዚህ በመገኘት የሃዘኑ ተካፋይ የሆናችሁትን ሁሉ ከልብ ያመሰግናል።